Sunday, November 15, 2015

የህዝብን ጥያቄ የይስሙላ በአልን በማክበር አይመለስም!!



ሰሞኑን የብአዴን አመራሮች የ35ኛ አመት የትጥቅ  የትግል በአል በሚል ለማክበር ሲሉ ያልሰሩትንና ሊሰሩ የማይችሉትን ነገር በመቀባጠርና በማልቀስ ህዝብን ለማሞኛት መሞከር ሰአቱን ያለፈባቸው ይመስላል።
በተለይ ደግሞ በአሁኑ ወቅት ለህዝብ ምንም ሳትሰራ ያለፉትን አመታት ብቻ መቁጠር ምንም ፋይዳ የለውም። ምክንያቱም ብአዴን/ኢህአዴግ የስልጣን ወንበሩን ከተቆጣጠርበት ጊዜ ጀሚሮ እስከ ዛሬ ደረስ ህዝቡ ለትግል ይዞት የተነሳ ጥያቄ ሳይመለስለት በመቅረቱ የተነሳ በስደትና በችግር በበረሃ ያለቀባሪ በቀረበት ወቅት ከህዝብ የወጣን ድርጅት ነን እየተባለ መናገር "ጅብ በማያውቁት አገር ሄዶ ቁርበት አንጥፍሉኝ" አለ እንደሚባለው ካልሆነ በስተቀር ሌላ ምንም ትርጉም ሊሰጠዉ አይቻልም።
ብአዴን የአማራን ህዝብ ወክያለሁ በማለት ከፌዴራል እስከ ሌሎች ክልሎችና ጋዜጠኞች በብአሉ በመጋበዝ የሰራነውን ታሪክ ተመልክታችሁ ለመላ የኢትዮጵያ ህዝብ አስተዋውቁልን ማለቱ አንድ ነገር ሆኖ በተለይም ከ35 አመታት የድርጅቱን ጉዞ በኢትዮጵያ ምን ለውጥ ተገኝቶነው ለሚለው ጥያቄ ግን መልሱ ግልፅ ይመስለናል።
ለመሆኑ በአሁኑ ጊዜ ህዝቡ በረሃብና በተለያዩ ችግሮች እየተሰቃየ ባለበት ወቅት እነሱ የብአዴን ምስረታ ቀን እንደ ትልቅ አጀንዳ ይዞዉ ከሦስት ወራት በላይ ስለ በአሉ ቅድመ ዝግጅነት ብዛት ያላቸዉ የአገሪቱ ታላላቅ አርቲስቶችንና ታዋቂ ሰዎች ይዞዉ ኑ መስክሩልን እያሉ ወድያ ወዲህ ሲሉ ለትራንስፓርት ለምግብ እንዲሁም ለዉሎ አበል  እየተባለ ከመንግስት ካዝና ያለ አግባብ እያባከኑ ነዉ። እንዲሁም በአሉን ምክንያት በማድረግ በልማታዊ መንግስታችን አስተዋፅኦ ያደረጉ እየተባሉ ብዙ ወጪ የተደረገበት ሽልማት በማዘጋጀት መሸለም ምን ተሰርቶ በህዝብ ላይ ምንስ አዲስ ለውጥ ስለ አመጡ ነዉ ግለሰቦችን  ለመሸለም የተነሳሱ? በምን አይነት የአእምሮ መለክያ ታስቦ ነዉ? ለሚለዉ የህዝብ ጥያቄ በብአሉ አመካይነት የተመለሰ አስመስሎ በማቅረብ ለፕሮፖጋንዳ እንዲመቻቸዉ የታቀደ ብቻ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው።
የብአዴን አመራሮች ብአሉን አስመልክቶ የተደረገ የሙህራኖች ወይይት ላይ ያላሰቡት ጥያቄ ሲቀርብባቸዉ የነበራቸው ህዝቡን ጥሩ እየመራን ነዉ የሚል ግንዛቤ የተሳሳተ መሆኑ ሊገነዘቡ በመቻላቸዉ በህዝብ ፊት ቀርበው ለመናገር እፍረት ሆኖባቸዋል።
አማራ ህዝብ እየተነሱ ያሉ አንገብጋቢ ጥያቄዎች፦
- የአማራ ህዝብ ችግሮች ሰሚ አጥተዉ በአሁኑ ወቅት ከማንኛውንም ብሔር በታች ሆኖ እየተሰቃየ ይገኛል?፤ በሃገሩ ለብዙ አመታት ሰርቶ ያፈራዉን  ንብረት እየተነጠቀ ከየክልሉ እየተባረረ ነዉ?፤ እናንተ ግን የአማራን ህዝብ ወክለናል እያላችሁ በየሚዲያው ስትናገሩ ለመሆኑ ለአማራ ህዝብ ምን የሰራችሁለት ነገር አለ ከደርግ በባስ መልኩ የአማራ ተወላጅ እየተዋረደና የመሰረተ ልማትና ቴክኖሎጂ ናፋቂ ሆኖ የተማረና ያልተማረ የተወለደበትን ቀየው በመልቀቅ ለስደት ተጋልጦ ይገኛል።
- የብአዴን መሪዎች በአማራ ህዝብ ስም እየነገዳችሁ ናችሁ እንጂ ከአማራ ህዝብ የወጣችሁ አይደላችሁም፤ የአማራ ህዝብ አስከፊ የደርግ ሰረአትን ለማስወገድ ከአጎራባች ክልሎች ጋር በመተባበር ግዜ የማይሸረዉ ታሪክ የሰራ ህዝብ እያለ፣ አሁን ግን እናንተ በምትሰሩት ሴራ የአማራን ህዝብ በድሮ ስርአቶች ታሪክ ተጠቃሚ ነው የነበረ በሚል የተሳሳተ አባባል ከአጎራባች  ክልሎች ህዝብ ጋር እየተፋጠጠ ባለበት በአሁኑ ሰአት ሰለ ኢትዮጵያ አንድነት እንዴት ይታሰባል፣ ለመሆኑ ለኢትዮጵያ አንድነትና የህዝብ ፍላጎት ለመመለስ የምታስቡ ከሆነ ለምን በኢህአዴግ ስር ብሄርተኝነትን የሚያባብስ ብሔራዊ የሆኑ 4 ድርጅቶችን ማቋቋም አስፈለገ?
የኢትዮጵያ ህዝብ በአሁኑ ጊዜ የሚፈልገዉ ያስነሳቸዉን ጥያቄዎችን ሰምቶ በተገቢ የሚመልስ አንድ ህዝባዊ ድርጅት እንጂ የአራቱ ድርጅቶች የህወሓት፤ የብአዴን፤ የደኢህዴንና ኦህዴድ ልደት በአል እየተባለ በየአመቱ ሽርጉድ እየተባለ ግዜና ገንዘብ መባከን በኑሮዉ ፋይዳ ስለ ሌለዉ ትርጉም የሚሰጠዉ አይደለም።  
ለመጠቃለል የብአዴን ስራ "ዶሮን ሲደሉሏት በመጫኛ ጧሏት" እንደሚባለው ከልሆነ በስተቀር የህዝብን ችግር በድርጅቱ ደካማ አመራር ይፈታል ብሎ መመኘት እራስን ከመገደል የሚለይ አይደለም። ምክንያቱም ይህ አስመሳይና  ጠባብ ራስ ወዳድ ቡድን በሚከተለዉ ቅጥ ያጣ ድርጅታዊ በአላትን የማክበር ጋጋታ የአገራችን ህዝቦች የሚያነሱትን ብሶትና ምሬትን የያዘ ጥያቄ  ስለማይፈታ።