Monday, December 19, 2016

የማይለወጡ ፤እንለወጣለን ባዮች!!



   የህዝብን ስልጣን በሃይል ቀምቶ በፌደራላዊ ስርዓት አገርንና ህዝብን እመራለሁ በሚል ፈሊጥ በስልጣን ላይ ተቆናጦ ያለው የኢህአዴግ ስርዓት፣በእነዚህ ባሳለፋቸው 25 ዓመታት ውስጥ ያስመዘገባቸውን የቁልቁለት ጉዞ በፀጋ ሊቀበላቸው ያስቸገሩትን ከባድ ውድቀቶችን አስተናግዷል።
    ይህ ስርዓት ገና ሲፀነስ ጀምሮ ችግር ቢኖረውም እንኳ ከፍተኛ ውድቀቶቹ ግን ከበረሃ ሽፍትነት ወጥቶ የከተማ ሽፍትነት ከጀመረ በኋላ ባለው እድሜው ነው ያስተናገዳቸው። ዛሬ ሙሉ በሙሉ ከህዝብ ነጥሎት ያለው ደግሞ ሊተገብራቸው የማይችል ቃላት ለወረት በመልቀቅ የአፈፃፀማቸው ሂደት ኪሳራ እያጋጠመው ስላለ ነው።
     ኢህአዴግ የሚናገራቸውና የሚገባቸው ቃል ኪዳኖች ተፈፃሚነት የሚያገኙ ቢሆኑ ኖሮ፣ይህ በአሁኑ ወቅት በአገራችን በመንግስትና በህዝብ መካከል ተፈጥሮ ያለው መግቻ የሌለው ፍጥጫ ባልተፈጠረ ነበር። ይህ ስርዓት ግን ቃሉን ሊፈፅም ባለመቻሉ የሚነሱትን የህዝብ ቁጣዎች ሁሌ በአፈሙዝ ኃይል እየጨፈለቀ የሚኖር ስለመሰለው እምቢተኝነት ያሳየውን ህዝብ በሙሉ እየጨፈጨፈው መጥቷል።
    ይሁን እንጂ የህዝብን ጥያቄና ድምፅ በሃይል አፍኖ ዘላቂነት ያለው ሰላም ለማረጋገጥ እንደማይቻል አረጋግጧል። ይህ ስርዓት የከፋው ይለጎም፣ እያለ ሲሄደው የቆየው መንገድ እንደማያዋጣው ስለተረዳ፣ ዛሬም ሊፈፅመው ወደማይችለው ተስፋ ቢስ ቃል ለመግባት ተገዷል። ከቃለ መሃላዎቹ አንዱ ደግሞ “በጥልቅ እንታደስ” “ህዝባዊ ወገንተኝነት ያለው ከህዝብ ጉሮሮ አይቀማም፣ወደ ብልሹ አሰራርም አይገባም” ወዘተ የሚል ነው።
   የዚህ ማስቀጠያ ደግሞ የማይለወጡ፥ እንለወጣለን ባዮች፣ መሆናቸውን እያወቁ እንለወጥ በማለት ከፌደራል ጀምረው እስከ ክልል መንግስታት ተሃድሶ የሚል ማር የተቀባ ቃል ተጠቅመው ከላይ እስከ ታች በተለያዩ ስብሰባዎች ሲጠመዱ እየታዘብን ነው። ይሁን እንጂ እነዚህ እየተካሄዱ ያሉት መድረኮች አዲስ ስላልሆኑ አዲስ ለውጥ ይዘው ይመጣሉ የሚል ቅንጣት ያህል እምነት ያለው ህዝብ የለም።
    ምናልባት በእነዚህ እየተካሄዱ ባሉት የተሃድሶ መድረኮች ሰው በሰው ሲተካ አቶ በዶ/ር ሲቀየር ታዝበናል። የኢትዮጵያ ህዝብ ወቅታዊ ጥያቄና ፍላጎት ግን ሰው በሰው ይተካ የሚል አይደለም። ጥያቄያችን እነዚህ አዲስ ተመራጮች እነማን ናቸው? ህዝባዊ ወገንተኝነት አላቸው ወይ? የህዝብ ችግር ይሰማቸዋል ወይ? የሚል ነው። አሁን ሲተኩ የምናያቸው ዶክተሮች ግን የስርዓቱ ታማኝ ካድሬዎችና አባላት ሆነው የቆዩ ናቸው።
    ከዚህ ባለፈ ኢህአዴግ በተለይ ህወሃት በእውነት ልትለውጥ የምትፈልግ ከሆነች፣እነዚህ አርጅተው አገልግሎታቸው አብቅተው ያሉትን ብቻ ሳይሆን ክልሉን ወደ ገደል እያመሩት ያሉት እነአባይ ወልዱ ፤ቅድሳን ነጋ፤ ኪሮስ ቢተውና ሌሎችም ለምን ለእነሱ ከማይበቃው ቦታ ያላስወገደቻቸው? መልሱን ለብዙሃኑ እንተወው? በመሰረቱ ግን ህወሃት ያካሄደቸው ተሃድሶ “ ግም ለግም ተያይዞ ኣዝግም” የሚለውን አባባል የሚያጠናክር ሆኖ ነው ያለፈው።
    የክልሉ ካቢኔ በተሸፋፈነና የህዝብ ውክልና በሌላቸው የስርዓቱ አባላት የተጠፈጠፈ ስለሆነ፣የህዝብን ኃላፊነት ሊዋጣና ህዝብ ሲጠብቀው ለነበረው ለውጥ በጥብቅ ሊገማገም አልቻለም። ለቀረበው ስም ሁሉ አጨብጭቦ ነው አፅድቆት ያለፈው። ይህ ደግሞ ህወሃት ምንያህል ፈላጭ ቆራጭ ሆኖ እንዳለ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የክልሉ ምክር ቤት አባላት የህወሃት አባል ሆነህ ህወሃትን መቃወም ራስን እንደመግደል አድርገው ነው አስረድተውን ያለፉት።
    ይህ ፍፃሜ ደግሞ ገና ከጅምሩ የታወቀ ቢሆንም እንኳ ህወሃት የማይለወጡ፥ እንለወጣለን ባዮች፣አባላቶቿን ከአንድ ወንበር ወደ ሌላ ወንበር እያሸጋገረች በስልጣን ለማርጀት የምትፈልግ ህዝባዊና አገራዊ ስሜት የሌላት ድርጅት እንደሆነች ያረጋገጠልን መድረክ ሆኖ ተጠናቋል።
    ህወሃት ይህን ሁሉ አድርጋም የህዝብን ቀልብ ለመሳብ አልቻለችም። አንድ ጊዜ የተቆጣ ህዝብ ያስከተለውን ማዕበል እንደቀድሞዋ በጠመንጃ ሃይል ለመግታት ስላልቻለች የአንድ መንግስት የመጨረሻ የውድቀት መግለጫ የሆነውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ልትተቀምበት ተገዳለች።
    ይህ ደግሞ ስርዓቱ ለማሳደድ በሚል ከሚወስደው የአይን የለኝም ጥርስ የለኝም እርምጃ ህዝባችን ለጊዜው ዝምታን ሊመርጥ ይችላል እንጂ፣ ዘላቂ መፍትሄ ሊሆን እንደማይችል አስቀድመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እርምጃ የወሰዱ አገራትን ተሞክሮ መመልከት ይቻላል። በመሰረቱ ግን “ የማይለወጡ፥ እንለወጣለን ባዮች” ስለፈከሩ ለውጥ ሊመጣ አይችልም።

No comments:

Post a Comment